July 31, 2019

ስኳር ምንድን ነው?

ስኳር ምንድን ነው? 

ጣፋጭ አታብዙ 
ለጤናዎ የሚጠቅሙ ፅሁፎችን ለማንበብ ገፃችንን ላይክ ያድረጉ

ስኳር ምንድን ነው? 

ስኳር የሚለው ቃል ገበታችን ላይ የምናገኘውን ነጩን ስኳር ብቻ ለማለት አይደለም፡፡ የተለያዩ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ መልኩ የምናገኛቸውን በቀላሉ የሚሟሙ ካርቦሃይድሬቶች ሁሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡

የተፈጥሮ ስኳር ምንድን ነው?


የተፈጥሮ ስኳር ማለት በተፈጥሮ በምግብ ውስጥ የምናገኘው ሲሆን ግሉኮስ፤ ፍሩትኮስ፤ ሱክሮስ ወይም መሰል በሆኑ ስሞች የሚጠራ ነው፡፡ለምሳሌ
 የላም ወተት ከተፈጥሮ የመጣ ላክቶስ የሚባል ስኳር አለው
 ሙዝ ከተፈጥሮ የመጡ ፍሩትኮስ፤ግሉኮስ እና ሱክሮስ የተባሉ የስኳር አይነቶችን ይዟል፡፡ ለዚህም ነው የሚጣፍጠው
 ካሮት ከተፈጥሮ የመጡ ፍሩትኮስ እና ግሉኮስ የተባሉ የስኳር አይነቶች ይዟል፡፡

ሰው ሰራሽ ስኳር ምንድን ነው?

ሰው ሰራሽ ስኳር ማለት በተፈጥሮ የምናገኘውን ስኳር በፋብሪካ ውስጥ አስተካክለን/ አምርተን ለገበታ ስናቀርበው ወይም ሌላ ምርቶችን ለማምረት ስንጠቀምበት ነው፡፡ በህንድ አካባቢ እና በአፍጋኒስታን ውስጥ በጥንት ዘመን መመረት የጀመረው ሰው ሰራሽ ስኳር ዛሬ ከገበታችን የማይጠፋ ሆኗል፡፡ ቡና ወይም ሻይ ለመጠጣት፤ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን ለማጣፈጥ፤ ኬክ እና ብስኩቶችን ለመጋገር የምንጠቀመው ይሄንን ሰው ሰራሽ ስኳር ነው፡፡ ሰው ሰራሽ ስኳር በአብዛኛው የሚመረተው ከሸንኮራ አገዳ ወይም ሹገር ቢትስ ከተባለ ተክል ነው፡፡

አብዛኛው ጊዜ ለምግብነት የምንጠቀምባቸው ጣፋጭ ነገሮች ሰው ሰራሽ ስኳር በብዛት አላቸው፡፡ለምሳሌ
 ደረቅ እና ለስላላሳ ኬኮች እና ኩኪሶች
 ታሽገው የሚሸጡ ብስኩቶች
 ለስላለሳ መጠጦች
 ከረሜላዎች፤ ሎሊፖፕ እና ቸኮሌቶች
 በቆርቆሮ፤ በፕላስቲክ ወይም በጠርሙስ ታሽገው የሚሸጡ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ወይም ጁሶች
 ለስላለሳ መጠጦች
 ታሽገው የሚሸጡ መጠጦች፤ ሃይል ሰጪ መጠጦች
 ታሽገው የሚሸጡ ምግቦች

ሰው ሰራሽ ስኳር ማብዛት ጉዳቱ ምንድን ነው?

የሰው ልጅ ለመኖር ወይም ለጤና ስኳር ግዴታ ያስፈልገዋል፡፡ የምንመገበው/ የምንጠቀመው የተፈጥሮ ስኳር ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ነገር ግን በቀን አንድ ወንድ ወይም ሴት ከ7 የሻይ ማንኪያ በላይ ስኳር ባይጠቀሙ ይመከራል፡፡ (ከአለም ጤና ድርጅት)

ሰው ሰራሽ ስኳር ማብዛት

1. ውፍረት ያመጣል፡- ሰው ሰራሽ ስኳር ረሃብን ያባብሳል፡፡ በተጨማሪም የምግብ ፍላጎታችን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡በሰውነታችን ውስጥ የሚመረት ሌፕቲን የተባለ ንጥረ ነገር አለ፡፡ ይሄ ንጥረ ነገር መጥገባችንን የሚነግረን እና የረሃብ ስሜትን የሚቆጣጠር ነው፡፡ ሰው ሰራሽ ስኳር ማብዛት ይሄ ሌፕቲን የተባለው ንጥረ ነገር በሰውነታችን ውስጥ በትክክል እንዳይሰራ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ መብላት ከሚገባን በላይ እንመገባለን፡፡

2. የሰውነታችንን የበሽታ መከላከል ችሎታ ያዳክማል፡- ከሚያስፈልገን በላይ ስኳር የምንጠቀም ከሆነ የተረፈው ስኳር ሰውነታችን በሽታዎችን በትክክል እንዳይከላከል ያደርገዋል፡፡ የተለያዩ አይነት ባክቴሪያዎች ይሄንን የተረፈ ስኳር እየተጠቀሙ በሰውነታችን ውስጥ ኢንፌክሽኖችን ሊፈጥሩም ይችላሉ፡፡

3. ብጉር ያመጣል፡- ሰው ሰራሽ ስኳር ማብዛት በደማችን ውስጥ የሚገኘውን የስኳር እና የኢንሱሊን መጠን እንዲያሻቅብ ያደርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰውነችን አስፈላጊ ከሆነው በላይ ወዝ እና አንድሮጅን የተባለ ንጥረ ነገር እዲያመርት ያደርገዋል፡፡በተጨማሪም ቆዳችን በቀላሉ ይቆጣል፡፡ ስለዚህ ብጉር እየተባባሰ ይመጣል፡፡

4. የስኳር በሽታን ያስከትላል፡- የሰው ሰራሽ ስኳርን የምናበዛ ከሆነ እና ለረጅም ጊዜም በዚህ ልምድ ከቀጠልን በሰውነታችን ውስጥ በጣፊያችን አማካኝነት የሚመረተው ኢንሱሊን በአግባቡ መስራቱን ያቆማል፡፡በዚህ ጊዜ በደማችን ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ያለአግባብ ይጨምራል ይሄ ማለት የስኳር ህመም ያዘን ማለት ነው፡፡

5. ቆዳችን ቶሎ እንዲያረጅ ያደርገዋል (ያስረጃል)፡- ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመን የቆዳ መሸብሸብ እንዲባባስ ያደርገዋል፡፡ ቆዳችን መሳብ እንዲችል እና ጥሩ ወዘና እንዲኖረው የሚያደርጉት ኮላጅን እና ኢላስቲን የተባሉትን ገምቢ የተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች ስኳር ያበላሻቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የቆዳችን መሸብሸብ ያለአግባብ ይፋጠናል፡፡

6. ለካንሰር ያጋልጣል፡- በ430,000 ሰዎች ላይ የተሰራ አንድ ጥናት የሚያሳየው ሰው ሰራሽ ስኳር ማብዛት ለሳንባ ካንሰር፤ ለምግብ ቧንቧ ካንሰር እና ለትንሿ አንጀት ካንሰር ያለንን ተጋላጭነት ከፍ ያደርገዋል፡፡

ማሳሰቢያ፡ አንዳንድ ሰዎች ክብደት ለመቀነስ ወይም ለጤና ብለው ሙሉ በሙሉ ስኳር መጠቀምን ሲያቆሙ ይስተዋላሉ፡፡ ይሄ በተገላቢጦሽ በሰውነታችን ውስጥ የስኳር እጥረትን ወይም ማነስን በማስከተል ችግር ሊያመጣ ስለሚችል አስፈላጊ የሆነውን ጥንቃቄ አድርጉ፡፡

ለጤናዎ የሚጠቅሙ ፅሁፎችን ለማንበብ ገፃችንን ላይክ ያድረጉ