July 31, 2019

7ቱ የአቡካዶ ጥቅሞች ለውበት

7ቱ የአቡካዶ ጥቅሞች ለውበት 

ለጤና 
ለአመጋገብ
ለውበት… 

አቡካዶ በብዙ ኮስሞቲክሶች ውስጥ ይገባል፡፡ በጥንት ዘመንም በአዝቴክ እና በማያ ስልጣኔ ዘመኖች የነበሩ ሴቶች አቡካዶን ለውበታቸው ይጠቀሙበት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ አቡካዶ (አቮካዶ) አመቱን በሙሉ በአብዛኛው በገበያ ላይ በተመመጣጣኝ ዋጋ እናገኘዋለን፡፡ አቡካዶ በውስጡ ተፈጥሯዊ የሆነ ቅባት፤ ሚኒራሎችን እና ቫይታሚኖችን ስለያዘ በቤታችን ውስጥ ከአቡካዶ የተለያዩ የውበት መጠበቂያዎችን መስራት እንችላን፡፡


1. እጅን ለማለስለስ፡- 

ከስራ ወይም ከተለያዩ ነገሮች የተነሳ እጃችን ሊሻክር ወይም ሊሰነጣጠቅ ይችላል፡፡ እጃችንን ለማለስለስ
አቡካዶ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
 ግማሽ ኩባያ የአቡካዶ ጁስ (በደንብ የላመ)፤ አንድ የእንቁላል ነጭ ክፍል (አስኳሉን መጨመር የለብንም)፤ አንድ የሾርባ ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ እና ሁለት የሾርባ ማንኪያ የአጃ ዱቄት አንድ ላይ በጎድጓዳ እቃ ውስጥ በደንብ ማደባለቅ
 ውህዱን እጃችንን መቀባት
 ከ30 ደቂቃ በኋላ እጃችንን በቀዝቃዛ ውሃ መታጠብ

2. የቆዳን መሸብሸብ ለመቀነስ፡-

 ከእድሜ፤ ከፀሃይ፤ ከአመጋገብ ወይም ከተለያዩ ነገሮች የተነሳ የፊታችን ቆዳ በቀላሉ ይሸበሸባል፡፡ ይሄንንም ለመቀነስ የፊት ማስክ ማዘጋጀት እንችላለን፡፡
 ሶስት የሾርባ ማንኪያ የአቡካዶ ጁስ (በደንብ የላመ) እና አንድ የሾርባ ማንኪያ የኮኮናት ዘይት አንድ ላይ በደንብ እናዋህዳለን
 ይሄንን ውህድ ንፁህ ፊት ላይ ቀብተን ከ30-45 ደቂቃ እንተወዋለን
 ከዛ ፊታችንን በፊት ሳሙና መታጠብ
 ይሄንን የፊት ማስክ በሳምንት ሁለት ቀን መጠቀም እንችላለን
 ከዚህ በተጨማሪም አቡካዶን መመገብ የፊትን መሸብሸብ ይከላከላል

3. ብጉርን ለመከላከል ወይም ለማጥፋት፡- 

አቡካዶ የፈታችን ቆዳ እንዳይቆጣ ከማድረግ በተጨማሪም ተፈጥሯዊ ቅባት ስላለው ቆዳችንን አያደርቅም፡፡
 ሶስት የሾርባ ማንኪያ የአቡካዶ ጁስ (በደንብ የላመ) እና አንድ የሾርባ ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ አንድ ላይ በደንብ እናዋህዳለን
 ይሄንን ውህድ ንፁህ ፊት ላይ ቀብተን ከ30-45 ደቂቃ እንተወዋለን
 ከዛ ፊታችንን በንፁህ ውሃ ብቻ መታጠብ
 ይሄንን የፊት ማስክ በሳምንት ሁለት ቀን መጠቀም እንችላለን

4. ለፀጉራችን ወዝ ለመስጠት፡- 

ፀጉራችን በተለያየ ምክንያት ይጎዳል በዚህም ምክንያት የተፈጥሮ ዛላ እና ወዘናውን ያጣል፡፡ አቡካዶ ለዚህ መፍትሄ ሊሆን ይችላል፡፡
 ግማሽ ኩባያ የአቡካዶ ጁስ (በደንብ የላመ)፤ አንድ የእንቁላል አስኳል (ነጩ የእንቁላል ክፍል መግባት የለበትም) እና ሁለት የሾርባ ማንኪያ የወይራ ዘይት አንድ ላይ በጎድጓዳ እቃ ውስጥ በደንብ ማደባለቅ
 ውህዱን ፀጉራችንን እና ቆዳችንን መቀባት
 ከ30-45 ደቂቃ በኋላ ፀጉራችንን በሳሙና/በሻምፖ በደንብ መታጠብ

5. ለፊታችን ቆዳ ወዝ ይሰጣል፡- 

ፊታችን ጥሩ ወዝ እንዲኖረው ይሄንን ማስክ መጠቀም እንችላለን፡፡ በተለይ ደግሞ ደረቅ የፊት ቆዳ ላላቸው ይሄ ማስክ ተመራጭ ነው፡፡
 ሁለት የሾርባ ማንኪያ የአቡካዶ ጁስ (በደንብ የላመ)፤ አንድ የሾርባ ማንኪያ እርጎ እና አንድ የሾርባ ማንኪያ ማር አንድ ላይ በጎድጓዳ እቃ ውስጥ በደንብ ማደባለቅ
 ውህዱን ፊታችንን መቀባት
 ከ15-30 ደቂቃ በኋላ ፊታችንን ለብ ባለ ውሃ ብቻ መለቀለቅ

6. ጥፍራችንን ያሳምራል፡- 

ጥፍራችን እየተሰባበረ የሚያስቸግረን ከሆነ እና ፈለግ የሚያስቸግረን ከሆነ አቡካዶ መፍትሄ ይሆናል፡፡
 ሁለት የሾርባ ማንኪያ የአቡካዶ ጁስ (በደንብ የላመ) ጥፍራችንን እና የጥፍራችንን አካባቢ እንቀባዋለን
 ከ20 ደቂቃ በኋላ በደንብ መታጠብ
 ጥፍራችንን እና አካባቢውን የወይራ ዘይት መቀባት

7. የአይንን ውበት ይጠብቃል፡- 

አንዳንድ ሰዎች ከአይናቸው ስር ያለው ቆዳ ይሸበሸባል ወይም ይጠቁራል ወይም ያብጣል፡፡ አይናችን ስር ያለውን ቆዳ ለማሳመር አቡካዶ መጠቀም እንችላለን፡፡ አቡካዶወን በስሱ ቆርጠን ጋደም ብለን ከአይናችን ስር ማስቀመጥ እና ከ20-30 ደቂቃ እዛው መተው፡፡

ለጤና
ለአመጋገብ
ለውበት…