July 30, 2019

የሮዝመሪ (የጥብስ ቅጠል) ሻይ እንደሚሆን ያውቁ ኖሯል?

የሮዝመሪ (የጥብስ ቅጠል) ሻይ እንደሚሆን ያውቁ ኖሯል?

አሰራሩ
 አንድ መካከለኛ ኩባያ ውሃ ማፍላት
 ውሃው ከፈላ በኋላ ግማሽ የሻይ ማንኪያ የሮዝመሪ ቅጠል (ደረቅ ወይም እርጥብ መሆን ይችላል) መጨመር
 እሳቱን ቀንሰን ለ5 ደቂቃ ማንተክተክ እና ማውጣት
 ውሃውን ማጥለል እና የሚቻል ከሆነ ትንሽ ማር ጨምሮ መጠጣት
 ይሄንን ሻይ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ እና በሳምንት ከሶስት ጊዜ በላይ እንዳንጠጣ ይመከራል፡፡

የሮዝመሪ (የጥብስ ቅጠል) ሻይ መጠጣት ለጤናችን ምን አይነት ጥቅም ይሰጣል?

1. ቆዳችን እንዳያረጅ ያደርጋል፡- በሮዝመሪ ሻይ ውስጥ የሚገኙት ፓይቶኬሚካልስ ቆዳችን እንዳይሸበሸብ ያደርጋሉ፡፡ በብጉር እና በፀሀይ ምክንያት ቆዳችን ላይ የሚፈጠሩ ጥቋቁር ምልክቶች እንዲጠፉ እና ፊታችን እንዲጠራ ይረዳል፡፡


2. የማስታወስ ችሎታን ያሳድጋል፡- በሮዝመሪ ሻይ ውስጥ የሚገኘው ካርኖሲክ አሲድ የተባለው ንጥረ ነገር የማስታወስ ችሎታችንን በማሳደግ እና የነርቮቻችንን ጤንነት በመጠበቅ የሚታወቅ ነው፡፡ እድሜያችን እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሚፈጠረውን የመርሳት ችግር እና ከመርሳት ጋር ተያይዞ የሚመጣውን አልዛይመረስ በሽታ ለመከላከል የሮዝመሪ ሻይ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

3. ካንሰርን ለመከላከል ይጠቅማል፡- በሮዝመሪ ሻይ ውስጥ የሚገኙት ሮዝማሪክ እና ካፊክ አሲዶች ካንሰርን ለመከላከል ይጠቅማሉ፡፡በተለይ ደግሞ ለትልቁ አንጀት ካንሰር፤ ለጡት ካንሰር እና ለደም ካንሰር መድሃኒት ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ጥናቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡

4. የምግብ መፈጨትን ያፋጥናል፡- በምግብ አለመፈጨት፤ በሆድ መነፋት፤ እና በሆድ ድርቀት ለሚሰቃዩ ሰዎች የሮዝመሪ ሻይ ፍቱን መድሃኒት ሊሆን ይችላል፡፡ የሮዘመሪ ሻይ አንጀታችን በማረጋጋት የሆድ መነፋት እና ጋዝን ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም በውስጡ ካርነሲክ አሲድ ስላለው በአንጀታችን ውስጥ ያሉትን ጤናማ ባክቴሪያዎች ያበረታታል፡፡

5. የበሽታ መከላከል አቅማችንን ያሳድጋል፡- በሮዝመሪ ሻይ ውስጥ እንደ ቫይታሚን ሲ፤ ቫይታሚን ኤ፤ ፖታሲየም፤ ማግኒዚየም እና ካልሲየም የመሳሰሉ ለጤንነታችን ጠቃሚ የሆኑ እና የበሽታ መከላከል አቅማችንን የሚያዳብሩ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ቫይታሚን ሲ የበሽታ መከላከል አቅማችንን ከማሳደጉ በላይ በባክቴሪያ እና በቫይረስ የሚመጡ በሽታዎችን ይከላከልልናል፡፡

6. የአይንን ጤና ይጠብቃል፡- በሳንፈርድ እና በርንሃም የምርምር ተቋሞች የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ በሮዝመሪ ሻይ ውስጥ ያለው ካርነሲክ አሲድ የተባለ ንጥረ ነገር የአይናችንን ጤና ይጠብቃል እንዲሁም ከእድሜ ጋር የሚመጣውን የአይን እይታ መቀነስ እነዲስተካከል ይረዳል፡፡

7. የሰውነት መቆጣትን ይቀንሳል፡- የሮዝመሪ ሻይ አንታይ ኢንፍላማቶሪ ነው፡፡ ማለትም በሰውነታችን ውስጥ የሚነሱ መቆጣቶችን/ህመሞችን ያስታግሳል፡፡ በተለይ ደግሞ በጡንቻዎቻችን፤ መገጣጠሚያዎቻችን እና በጅማቶቻችን ላይ የሚነሱ ህመሞችን ለማስታገስ እና ለማዳን ጠቃሚ ነው፡፡

8. የአፋችንን ጠረን ጥሩ ያደርግልናል፡- በአፋችን ውስጥ ባሉ ባክቴሪያዎች ምክንያት የአፋችን ጠረን መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡የሮዝመሪ ሻይ መጠጣት ግን እነዚህን ባክቴሪያዎች ከአፋችን ውስጥ ያጠፋል፡፡ ስለዚህ የአፋችንን ጠረን እና የአፋችን ጤና ይስተካከላል፡፡

9. የስኳር መጠናችንን ያስተካክላል፡- የሮዝመሪ ሻይ ውስጥ ካምፊን፤ ካርኖሶል እና ሉቲሊን የተባሉ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች የልባችንን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር በሰውነታችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ያስተካክላሉ፡፡ በተጨማሪም የደም ግፊታችን እንዲስተካከል ያደርጋሉ፡፡

የሮዝመሪ የጎንዮሽ ጉዳት
 አንዳንድ ሰዎች ለሮዝመሪ አለርጂክ ሊሆኑ ስለሚችሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እንደ አስፕሪን ላሉ መድሃኒቶች አለርጂክ የሆነ ሰው ለሮዝመሪም አለርጂክ ሊሆን ይችላል፡፡
 የደም ግፊት መድሃኒቶችን፤ የደም ማቅጠኛ መድሃኒቶችን፤ የስኳር ህመም መድሃኒቶችን እና የልብ ህመም መድሃኒቶችን የሚወስዱ ከሆነ የሮዝመሪ ሻይ ከመጠጣቶ በፊት ሀኪም ማማከር ይኖርቦታል፡፡
 የሮዝመሪ ሻይ ለእርጉዝ ሴቶች እና ለሚያጠቡ ፍፁም የተከለከለ ነው፡፡
 የሮዝመሪ ሻይ የሚጥል በሽታ ላለባቸው ሰዎች አይመከርም፡፡ የነርቭ ወይም የአእምሮ መድሃኒቶችን የሚወስዱ ከሆነ የሮዝመሪ ሻይ ከመጠጣቶ በፊት ሀኪም ማማከር ይኖርቦታል፡፡

ለጤንነቶ የሚጠቅሙ ፅሁፎችን ለማንበብ እባኮትን ገፃችን ላይክ ሼር ያድረጉ