የኮሌራ ወረርሽኝ አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ ሶማሌና አማራ ክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱን የኢትዮዽያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ::
በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ እና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ህመም ህክምና እያገኙ ካሉ 5 ሰዎች ውስጥ አንዱ በላብራቶሪ ቪብሮ ኮሌራ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ለሁሉም ህክምና እየተሰጠ እንደሚገኝ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል::
በተመሳሳይ መልኩ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ህመም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይና ሶማሌ ክልሎች በአጠቃላይ በ360 ሰዎች ላይ የታየ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 8 የሚሆኑት በላብራቶሪ የኮሌራ በሽታ መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል::
እንደ ኢቢሲ ዘገባ ሁሉም አስፈላጊውን ህክምና እያገኙ ሲሆን በቅርቡ ለበሽታው
በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የክትባት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ኢንስቲትዩቱ
አብራርቷል::
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህንን በመገንዘብ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግና ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ህክምና ማግኘት ይኖርባቸዋል ተብሏል::
በበሽታው የተያዘ ሰው በተደጋጋሚ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ይኖረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የሰውነት ፈሳሽና ጠቃሚ የሆኑትን ንጥረ ነገሮች መጠን ያዛባል፡፡
በተጨማሪም
• አጣዳፊ መጠነ ብዙ የሆነ ውኃማ ተቅማጥ
• ትውከትና ቁርጥማት
• የአይን መሰርጐድ
• የአፍና የምላስ መድረቅ
• እንባ አልባ መሆን
• የሽንት መጠን መቀነስ
• የቆዳ ድርቀትና መሸብሸብ በመጨረሻም ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ድርቀት በማስከተል ህመምተኛው በወቅቱ ካልታከመ ለሞት ሊያበቃው ይችላል፡፡
መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች
• መፀዳጃ ቤት መገንባትና በአግባቡ መጠቀም
• ምግብን በሚገባ አብስሎ መመገብ
• በውኃ /መድኃኒት/ በውኃ አጋር/ የታከመ ውሃ ለመጠጥ መጠቀም ወይም ውኃ አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠጣት
• እጅን በውኃና በሳሙና /በአመድ በደንብ አጥርቶ መታጠብ
• ከመፀዳጃ ቤት መልስ መታጠብ
• ምግብ ከማዘጋጀትዎ በፊት መታጠብ
• ምግብ ከመመገቦ በፊትና በኋላ በደንብ መታጠብ
• ህጻናትን ካፀዳዱ በኋላ መታጠብ
ማንኛውም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ አካባቢን ወይንም ውኃን እንዳይበክል በአግባቡ ማስወገድ፡፡ ምልክቱ የታየበት ህመምተኛ ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ሊታከም ይገባል፡፡