July 30, 2019

ለራስ ምታት ፍቱን የሆኑ 9 የምግብ አይነቶች

ለራስ ምታት ፍቱን የሆኑ 9 የምግብ አይነቶች


1. ዝንጅብል
ዝንጅብል ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ገና በቅርቡ የተጀመሩ ቢሆንም በውስጡ የደም ቧንቧዎችን መቆጣት እና ህመም የሚቀንሱ መድሃኒቶች ውስጥ ካሉ ኬሚካሎች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ተመራማሪዎች ማግኘት ችለዋል፡፡ በተለይ በከባድ የራስ ምታት ወቅት የደም ቧንቧዎችን መቆጣት በማስከተል ራስምታቱ እንዲቀሰቀስ የማድረግ ተግባር ያላቸውን ፕሮስታግላንዲን የሚሰኙ ንጥረ ቅመሞች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ራስ መታቱን እንደሚያስታግስ የሪደርስ ዳይጀስት መጽሔት ይገልጣል፡፡ ራስ ምታቱን ሙሉ በሙሉ ባያቆመው እንኳ ከራስ ምታት ጋር የሚመጡ ደስ የማይሉ እንደ ማቅለሽለሽ አይነት ስሜቶችን በቶሎ ይቀንሳል፡፡ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ኢትዮጵያውያን ያለጥናቶቹ ውጤትም ቀድመው ለሆድ ህመም እና ማቅለሽለሽ ዝንጅብል አኝክበት ሲሉ የኖሩት!


2. ሃብሃብ
ሃብሃብ - በውስጡ እጅግ ብዙ ፈሳሽ እና ማዕድናትን የያዘ ከፍራፍሬዎችም በትልቅነቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ወደ ናዝሬትና ሐዋሳ መስመር ሲሄዱ በመንገድ ዳር ተሸክመው ሲሸጡት እንመለከታለን፡፡ ሞክረውት እንደሆነ ባላውቅም በጉዞው ወቅት ለሚኖረው ሙቀት እና የውሃ ጥም ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጥቅሙም ባሻገር ለራስ ምታት ፍቱን መድሃኒት መሆኑ በባለሙያዎች ተጠንቶ ተቀምጧል፡፡ የሪደርስ ዳይጀስት መጽሔት በቅርቡ ባሰፈረው ጽሑፍ ሃብሃብ ለራስምታት ፍቱን ያስባለው ከፍተኛ የውሃ እና ማዕድናት በተለይም ከፍተኛ የማግኒዚየም ማዕድን መጠኑ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለራስምታት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ድርቀት ወይም በሰውነት ውስጥ በቂ ፈሳሽ ያለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ፍራፍሬ ደግሞ ይህን ችግር በደንብ ይፈታል፡፡ ከራስ ምታት ክኒን ይልቅ በቅርብ ሃብሃብ ከተገኘ በደቂቃዎች ውስጥ ከራስምታቱ እረፍትን ይሰጣል ብለው ባለሞያዎቹ ይናገራሉ፡፡

3. ቡና
ለአንዳንዶች ቡና ፍቱን የራስ ምታት መድሃኒት ሲሆን ማይግሬይን ላለባቸው አንዳንድ ሰዎች ላይ በብዛት ሲወሰድ ማይግሬይኑን የሚቀሰቅስበት አጋጣሚ አለ፡፡ ሳይንሱ ሁሉንም የቡና ምስጢር ፈትቶ ባይጨርስም እስካሁን ባሉት ጥናቶች መሰረት ግን ቡናን ፍቱን የራስ ምታት መድሃኒት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ መጠኑን በልክ ማድረግ አብሮ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለከባዱ የራስ ምታት ማይግሬይን የሚታዘዙ ክኒኖች ውስጥ የቡና ዋና ንጥረ ነገር ካፌይን ይገኛል፡፡ ስለሆነም ቡና ለራስ ምታት በመፍትሄነት መቅረቡ አስደናቂ ነገር አይሆንም፡፡ ይሁንና መጠኑ በበዛ ቁጥር ራስ ምታትን ከማስታገስ ይልቅ ጭራሽ ሊቀሰቅሰው ይችላል፡፡ እጅግም ወፍራም ያልሆነ አንድ ወይም ሁለት ስኒ ቡና ከሁለት ክኒን የተሻለ ተፈጥሯዊ መድሃኒት ሆኖ ተገኝቷል፡፡

4. ስፒናች
ትኩስ ስፒናች ጎመን ቅጠል በውስጡ የያዛቸው ቅመሞች ራስ ምታትን በማስታገስ ብቻ ሳይሆን የደም ግፊት መጠንን በመቀነስም በቀደመው ጊዜ ጥቅም እንደነበራቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ በርካሽ ለሚገኝባቸው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ይህ ጥሩ ዜና ይመስላል፡፡ በውጪው ዓለም ስፒናችን አብስሎ ወይም በትኩሱ ከቲማቲም ጋር ከትፎ በመብላት ብቻ ሳይሆን ጨምቆ ከመጠጣትም ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ደግሞ ይህ ፍቱን አትክልት ለራስ ምታትም ፈጣን መፍትሄ ይሰጣል ብለዋል፡፡ ቢፈልጉ ጨምቀው ከሻይ ጋር አለዚም ባዶውን ወይም ትኩሱን ቅጠል ሰላጣ እንደሚያዘጋጁት አዘጋጅተው ቢመገቡት ከራስ መታቱ ፋታ እንዲያገኙ እንደሚረዳዎት የተደረጉ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም

5. ሙዝ፣
6. እርጎ፣
7. ጉበት፣
8. ድንች እና
9. ቃሪያም ራስ ምታትን በመቀነስ በኩል ፍቱን እንደሆኑ በጥናት ተረጋግጥዋል፡፡