July 31, 2019

ለመጥፎ አፍ ጠረን 6 የቤት ውስጥ መፍትሄዎች

ለመጥፎ አፍ ጠረን 6 የቤት ውስጥ መፍትሄዎች

መጥፎ የአፍ ጠረን የምንለው በሽታ ሃሊቶሲስ በመባል ይታወቃል ። በሰዎች መሃል የሚያሸማቅቀን በሽታ ሲሆን በራስ መተማመናችን ላይ ጉዳት አለው ። መጥፎ ሽታ ብዙ መንስኤዎች አሉት ። ጠረን ያላቸው ምግቦች መመገብ ፣ ማጨስ ፣ የአፍ መድረቅ ፣ የድድ በሽታ ፣ የሳይነስ በሽታ እና ሌሎች በሽታዎች የአፍ ጠረን ሊያመጡ ይችላሉ።

ዋናው የመጥፎ አፍ ጠረን መነሻ አፋችን ጀርባ ወይም በጥርሶቻችን መሃል የሚገኝ የባክቴሪያ ክምችት ነው። ሽታን ለመከላከል የአፍ ጤንነትን መጠበቅ ይኖርብናል ። ጥርስን በየግዜው መቦረሽ ፣ በቂ ውሃ መጠጣት ሌላኛው መፍትሄ ሲሆን ምግብ ከተመገቡ በኋላ አፋችንን መጉመጥሞጥ በጥርሳችን መሃል ያሉ የምግብ ፓርቲክሎችን ለማስወገድ ይረዳል ።
ሌሎች ለአፍ ጠረን ልናውላቸው የምንችላቸው የቤት ውስጥ መፍትሄዎች ይከተላሉ ።


1) ቀረፋ

ቀረፋ በውስጡ ሲናሚክ አልዲሃይድ አሲድ የያዘ ሲሆን ይህ ዘይት መጥፎ ሽታን ከመሸፈን አልፎ አፋችን ውስጥ ያለውን የባክቴሪያ መጠን በመቀነስ ይታወቃል። መጥፎ የአፍ ጠረንን ለመቀነስ እንደሚከተለው ማድረግ ይችላሉ ፦
አንድ የሻይ ማንኪያ የቀረፋ ዱቄት አንድ ብርጭቆ ውሃ ውስጥ አድርገው ያፍሉ ውሃውን አጥልለው ይጉመጥመጡበት፡፡

2) የፐርስሊ ቅጠል

ፐርስሊ ውስጥ ያለው ክሎሮፊል መጥፎ የአፍ ሽታን ለመቀነስ ይረዳል። የፐርስሊ ቅጠል አቸቶ ውስጥ ነክረው ማላመጥ
እንደ ሌላ አማራጭ የፐርስሊ ቅጠሉን ፈጭተው ጁሱን ቀስ ብለው መጠጣት

3) የሎሚ ጭማቂ

የሎሚ አሲዳማ ይዘት ጥርስዎ ውስጥ የባክቴርያ እድገት እንዲገታ ይረዳል። የሎሚ ሽታም እራሱ የአፍዎን ጠረን ለመከላከል ይረዳል ።

1 ሻይ ማንኪያ የሎሚ ጭማቂ ውሃ ውስጥ ጨምቀው አማስለው ይጉመጥመጡበት ። ጨው ጨምረውም መጉመጥሞጥ ይችላሉ። ይህ መፍትሄ የአፍዎን ድርቀት በመቀነስ በአፍ ድርቀት የሚመጣን ሽታ ለመቀነስ ይረዳል ።

4) የፖም አቸቶ (አፕል ሲደር ቬኒጋር)

ይህ አቸቶ የፒኤች መጠን የማመጣጠን ባህሪው ስላለው ለመጥፎ የአፍ ጠረን መፍትሄ እንዲሆን ይረዳል ፡፡
አንድ ሻይ ማንኪያ የፖም አቸቶ ከአንድ ብርጭቆ ውሃ ጋር አቀላቅለው ከምግብ በፊት ይጠጡ ፡፡›

5) የመጋገሪያ እርሾ

የመጋገርያ እርሾ መጥፎ ሽታ በማስወገድ ይታወቃል። መጥፎ ጠረን የሚያስከስተውን የአሲድ አለመመጣጠን በማሻሻል የአፍ ጠረናችንን ይቀንሳል ። የአፍ ውስጥ ባክቴሪያ በመዋጋት መጥፎ ሽታን ያስቀራል።

ግማሽ የሻይ ማንኪያ እርሾ አንድ ብርጭቆ ውሃ ውስጥ አቀላቅለው በቀን አንዴ ይጉመጥሞጡ ፣ ጥርስዎን በእርሾ መቦረሽ ያፍዎን አሲዲቲ ይቀንሳል ባክቴሪያ እንዳያድግም ይከላከላል፡፡

6) ሻይ

ኖርማልም ሆነ የቅጠላ ቅጠል ሻይ የአፍ ጠረን ለመከላከል ይጠቅማሉ። አረንጓዴ ሻይ ውስጥ ያለው አንቲኦክሲዳንት ፖሊፌኖልስ ባክቴርያ አፋችን ውስጥ እናዳይድግ ይከላከላል።

ከላይ የጠቀስናቸውን ተጠቅመው ምንም መፍትሔ ካላገኙ የአፍጠረኑን ያመጣው ሌላ መንስኤ ሊሆን ስለሚችል ሀኪም ያማክሩ ፡፡